});

ታሪካዊ ኃላፊነት ለታሪካዊ ወቅት፣ቄሮ በራሱ ማመንና መደራጀት አለበት!

የወቅቱ ተግዳሮቶች ወቅታዊ ምላሽ ይጠይቃሉ። ታሪካዊ ወቅት ታሪካዊ ኃላፊንትን ትውልዱ ላይ ይጥላል። ያለንበት ወቅት ውሳኝና ታሪካዊ ወቅት ነው። ወጣቱ በመስዋዕትነቱ የሕወኅትን አገዛዝ ከሥልጣን ማዕከል በመግፋት ወደዳር ገፍትሮታል። በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎችን እንዲደፋፈሩ በማድረግ በሕወኅት ለይ የበላይነትን እንዲጎናፀፉ ረድቶአል። ነገር ግን እስካሁን ጥያቄዎቹ አልተመለሱም። በእርሱ መስዋዕትነት ሥልጣንን የተጎናፀፉት ድርጅቶች (ኦዴፓና አዴፓ) የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ጥቅም ወደጎን በመተው፣ አትኩሮታቸውን የራሳቸውን ስልታዊ ትግልና ድል ወደ መከተል መልሰዋል። የራሳቸውን ሥልጣን የማጠናከርን ሥራ ቅድሚያ ሰጥትው እየሰሩ ነው። የቅርፅና የአደራረግ (ወይም የstyle) ለውጥ ላይ ብቻ በማተኮር ይዘት ያለው፣ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስና ፖለቲካዊ ቋጠሮዎችንም ለመፍታት የሚያስችል ጥረት ከማድረግ ታቅበዋል፣ ወይም ራዕይና አቅም አጥተዋል። መሠረታዊ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ተቃርኖዎቹን በመሸፋፈን (ወይም የሌሉ በማስመሰል) በ"ፍቅርና ይቅርታ" ስብከት ለማለፍ እየሞከሩ ነው። መሪዎቹም (ለምሳሌ ዶር አብይ፣ አቶ ለማ፣ ከንቲባ ታከለ)፣ በአገሪቱ የአደባባይ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ፖለቲካዊ እውነቶችን እንዳሉ ተናግረው፣ የነዚህ (መራራ) እውነቶች ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ከነ መራራ እውነቱ በፍቅር የማቀፍ፣ የመቀበልና፣ የማካተት የሞራል ብርታት ከማሳየት ወደ ሽንገላና ድለላ አፈግፍገዋል። ይሄ ደሞ የአገሪቱ ፖለቲካ ከነህመሙ እንዲቀጥልና አሁንም በየቀኑ እያመረቀዘ እንዲያደማን እያደረገ ይገኛል። እነዚህ መሪዎች፣ ስለአገራዊ ማንነታችን፣ ስለብሔር-ተኮር ጭቆና፣ ስለ ብሔሮች የወል መብቶች፣ ስለ ሰንደቅ ዓላማ፣ ስለአገሪቱ አወቃቀርና ፌዴራሊዝም፣ ስለ አገራዊ የሥራ ቋንቋዎች፣ ስለ አገሪቱ ዋና ከተማ፣ ስለ መሬት ባለቤትነት፣ ስለ ክልሎች ወሰን፣ ስለ ፊንፊኔ ወሰንና በከተማው ላይ ኦሮሞ ስላለው መብትና ጥቅም፣ ስለሕዝቦች የማንነትና የክልልነት ጥያቄ፣ ወዘተ... አምታች፣ ግልፅ ያልሆነና ወላዋይ አቋም በማሳየት በሕዝቦች ዘንድ ጥርጣሬ፣ አለመተማመንና አላስፈላጊ ፉክክር እንዲበራከት አድርገዋል። ሌላው ቀርቶ በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች፣ በማሻሻያ መንገዶቹና አሰራሮቹ ላይ እንኳን ግልፅ የሆነ ሕገ-መንግስታዊ አካሄድ ለመሄድ ቁርጠኝነት አያሳዩም። ... በተለይ የኦሮሞ ሕዝብን የመብት ጥያቄዎች በማድበስበስ፣ እንዲያውም በተቃራኒው የኦሮሞ ሕዝብን ብሔራዊ ሕልውና የሚገዳደርና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል። ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ እለት ተእለት ለሞትና ለእልቂት እየተዳረገ ይገኛል። በያለበት የሕይወት ደህንነትና የነፃነት መብት እያጣ ነው። "ግድያና ዕልቂት ይቁምልን" ከመፈክርነት ይልቅ የየዕለቱ የልመና ቃል ሆኗል። የክልሉ ድንበሮች/ወሰኖች ከሁሉም አቅጣጫ በጥቃት ሥር ወድቀዋል። ከሱማሌ ክልል ጋር የሚጋራው ረጅሙ ወሰን በአብዲ ኢሌ ልዩ ኃይል ተጠቅቶ 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል። አሁንም ቀጥላል። ወሰኑም አልተካለለም። ለማካለልም (ቢያንስ የ97/98ቱን ሬፈሬንደም ውጤት) ለማስተግበር ጥረት ሲደረግ አይታይም። በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ልዩ ኃይል ጥቃት ተሰንዝሮ ሕዝብ አልቋል፣ ተፈናቅሎአል፣ አሁንም በእንግልት ላይ ነው። በፌደራልም በክልልም የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ኦዴፓ፣ ጥቃቱን ለማስቆም በቂ ጥረት ካለማድረጉም ባሻገር፣ የክልሉን ድንበር/ወሰን በግልፅ አስቀምጦ ለማስከበር አልቻለም። ለጊዜው ግልፅ የወጣ የኃይል እንቅስቃሴ አይኑር እንጂ ከጋምቤላ፣ ከአማራና ከደቡብ ክልሎች ጋርም የወሰን አለመግባባቶች እንዳሉ ይታወቃል።እነዚህን ሁሉ መርህ-አዘልና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ባለመሆኑ አንዳንድ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት የሆኑ ጀብደኛ ፖለቲከኞች "ክልሉን እናፈርሳለን" የሚል ዛቻቸውን የሰርክ ተግባር አድርገውታል። የፊንፊኔ ከተማ መስተዳድርም ከሕጋዊ ሥልጣኑ ወሰን ውጪ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየገባ ግንባታ እየሰራ ድንበር/ወሰኑን እያሰፋ ኦሮሞ ገበሬዎችን እያፈናቀለ ይገኛል። ይሄም ኦሮሞዎችን መሬት የለሽ፣ ቤት የለሽ፣ መተዳደሪያ የለሽና መድረሻ-ቢስ ንቅል ማህበረሰብ እያደረገ ይገኛል። በከተማም ሆነ በክልሉ ዳርቻዎች የሚደረጉ መስፋፋቶች የኦሮሚያን ግዛታዊ ህልውና (territorial existence) ጥያቄ ውስጥ እያስገቡት ይገኛሉ። ለዚህ አደጋ ኦዴፓ በቂ ምላሽና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ተስኖታል። ወጣቱ 'የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው' ብሎ ያነሳቸውና የህይወት፣ የአካል፣ የነፃነት፣ እና የዕድሎች መስዋዕትነት የከፈለባቸው ጥያቄዎቹ አለመመለሳቸው ሳያንስ፣ (ከዛሬ ነገ የዶር አብይና የአቶ ለማ መንግሥት ይመልስናል እያለ በትዕግስት ቢጠብቅም) መንግሥት ጥያቄዎቹን እያድበሰበሳቸውና እየቀበራቸው ይገኛል። የአገር ባለቤትነት ጥያቄው፣ በክልል እራስን በራስ የማስተዳደርና አገርን በጋራ የማስተዳደር ጥያቄው፣ የመሬት (እና ከመሬቱ አለፍትህ ያለመፈናቀል) ጥያቄው፣ የማንነት፥ የቋንቋ እኩልነት፥ የባህል ፍትህ ጥያቄው፣ በከተማው ላይ የባለቤትነት ጥያቄው፣ የድንበር ይከበርልኝ ጥያቄው፣ የፍትሃዊ የሃብት፣ የሥልጣንና የዕድሎች ክፍፍል ጥያቄው፣ በአጠቃላይ የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎቹ ሁሉ ተረስተዋል፣ ተድበስብሰዋል፣ ወይም ስልታዊ በሆነ ሁኔታ ተቀብረዋል። ትውልዱ፣ በተለይ የለውጡ አማጭ ኃይል የሆነው ቄሮ፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የማየት ተስፋው ከዕለት ዕለት እየደበዘዘ ይገኛል። በሥልጣን ላይ ያለው የኦዴፓ-አዴፓ መንግሥት ነፃ፣ ፍትሃዊና ፉክክር ያለበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ ዴሞክራሲያዊት አገርና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኝነት ማሳየት ተስኖታል። የፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ በመፍጠርና የወደፊቱ አቅጣጫ ላይ ግልፅ የሆነ ውይይት (እንደአስፈላጊነቱ ድርድርም) በማድረግ የሽግግር ሂደቱን ከማሳለጥ ይልቅ እስካሁን የነበረውን ኢሕአዴግ በሥልጣን በማቆየት ሥርዓቱን ለማስቀጠል በመጣጣር ላይ ይገኛል። ለኦሮሞና ለሌሎች ብሔሮች የወል መብቶች ግልፅ ጥላቻ ያላቸውንና ከፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ ያልሆኑ ሰዎችን (እንዲያውም የእነዚህ ፓርቲዎች መሪ የነበሩ ግለሰብን)፣ ያለ ፓርቲዎች ምክክር፣ በምርጫ ቦርድ ኃላፊነት በመሾም የዴሞክራሲያዊ ምርጫን ተስፋ አጨልመውታል። ይሄ ሁሉ ሲሆን የኦሮሞ ሕዝብ በሂደቱ ውስጥ ድምፅና ውክልና እንዲያጣ ሆኗል። የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው ኢሕአዴግን መደገፍን አማራጭ እንደሌለው ሥራቸው አድርገው የወሰዱት መስለዋል። አንዳንዶቹም ሁኔታው ባይመቻቸውም በግልፅ የሕዝባቸውን ፍላጎት በመግለፅና ጥቅሙንና መብቱን የሚያስጠብቅ ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ በሂደቱ ላይ ጫና ማሳደር አልቻሉም። ሕዝቡ ግራ ተጋብቶ ባለበት ሁኔታም አመራር በመስጠትና የተግባር ፕሮግራም በመንደፍ ሕዝቡን ማታገል አልቻሉም። እስካሁን ሁለት ዘግናኝ ግድያዎች በኦሮሞዎች ላይ ሲፈፀሙ (በመስከረም ወር በፊንፊኔና ዙሪያዋ፣ ሰሞኑን በምዕራብ ኦሮሚያ) ብቻ ይሄንኑ በመኮነን መግለጫ ከማውጣት የዘለለ እርምጃ ሲወስዱ አልታዩም። ወጣቱ፣ ታግሎ በመስዋዕትነቱ (አንፃራዊ) ድል ባገኘ ማግስት ያለ መሪ፣ ሕዝቡም ያለ ድርጅታዊ ጥላ ከለላ መቅረቱ ግልፅ ሆኗል። ዛሬ ሁሉም የድርጅት መሪዎች ከእስር ቤት ወጥተው በነፃነት መንቀሳቀስ በሚችሉበት ወቅት፣ ዛሬ ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከስደት ተመልሰው በሕዝባቸው መካከል በሚገኙበት ወቅት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ያለ መሪ፣ ያለ ወኪል፣ ያለ ድምፅ፣ ያለ ተሟጋች ድርጅት መቅረቱ ሁኔታውን በእጥፍ አሳዛኝ ያደርገዋል። ሰሞኑን የአዴፓ መሪዎች በዋሽንግተን ዲሲ ግልፅ እንዳደረጉት የዶር አብይ የሚመራው የኦዴፓ አመራር የሚያስጠብቀው ጥቅም ወይም የሚወክለው ሕዝብ የአማራ ክልልን ሕዝብ እንደሆነ ነግረውናል። እኛም ይሄንኑ እውነታ ለወራት በተግባር ስንታዘብ ቆይተናል። (የአማራ ሕዝብ ይሄን ያህል በነርሱ ሲተማመን የኦሮሞ ሕዝብ ይሄን ያህል ሊተማመንባቸው አለመቻሉ እራሱ የኦሮሞ ህዝብ መብትና ጥቅምን በመወከል ክፍተት እንዳለባቸው ያሳያል። ኦዴፓዎች ይሄንን ሁኔታ የወዳጅ ማብዣ ስልት እንደሆነ ቢናገሩም፣ ወዳጅ ማብዛት የራስን መብትና ጥቅም ቀብረው ሳይሆን መብታቸውን እያስከበሩ መርህ-መር ግንኙነት በመፍጠር እንደሆነ ማንም አይስተውም።) ቄሮ፣ በቀደሙት ጊዜያት ሕዝቡን ሊወክሉት የሚችሉ ድርጅቶችና መሪዎቹ በእስርና በስደት ላይ በመሆናቸው ድርጅት መመስረት ሳያስፈልገው በብሔራዊ አንድነት ስሜት ሲታገል ቆይቷል። በዚህ ወቅት በአብዛኛው፣ አክቲቪስቶች በሚያስቀምጡት አጠቃላይ የትግል አቅጣጫ ላይ በመመርኮዝ ሲታገል ቆይቷል። ተስፋው፣ አንድ ቀን እነዚህ ከእስርና ከስደት የተመለሱ መሪዎቹ አመራር እየሰጡት የሕዝቡን የዘመናት ትግል ከግብ ያደርሱታል የሚል ነበር። አሁን ያለው ሁኔታ ይሄን አያሳይም። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአመራር ክፍተት በመኖሩ የትግሉን ፍሬና ግብ ለሌሎች አሳልፎ ሰጥቶ፣ ብቁ የሆነ ድርጅታዊ ጥላ በማጣቱ ብቻ፣ በግራ መጋባት ውስጥ ገብቶ ይገኛል። ቄሮ፣ ለመታገልና ለመስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን በራሱ እንደ ፖለቲካ ኃይል ተደራጅቶ፣ ሥልጣንን ተናጥቆ፣ የሞተለትን፣ የደማና የቆሰለለትን ቅዱስ ዓላማ (ከሌሎች የአገሪቱ ተራማጅ ኃይሎች ጋር በጋራና በተናጥል፣ በአጋርነትና በትብብር፣ በክልልና በአገር ደረጃ) የማስፈፀም ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆበታል። ይሄን ለማድረግ ብቃቱም፣ ዝግጅቱም፣ ልምዱም አለው። ያለፉት 7-8 ወራት እንዳሳዩት ዛሬ የሚያስፈልገው በአሰራሩ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ እና ከህዝብ ጋር ቅርብ ቁርኝት ያለው (connected የሆነ)፣ በአስተሳሰቡ ግትር (doctrinaire) ያልሆነ፣ በስልቱና ስትራቴጂው ነባራዊ እውነታ ለይ የተደገፈ (pragmatic)፣ የራዕይና የተልዕኮ ግልፅነት (clarity of vision and mission) ያለው፣ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የተሻለ የወደፊት ሕይወትን ለመፍጠር (a better and an alternative future ለመገንባት) የሞራል ብርታትና ጥንካሬ (moral courage) ያለው አመራር ነው። ቄሮ፣ ይሄንን ዓይነት አመራር እራሱ ውስጥ በብዛት እንዳለው እሙን ነው። ያለንበትን ወቅት ታሪካዊነት በመረዳት፣ ለታሪካዊ ኃላፊነት በመዘጋጀት መንፈስ፣ በእራሱ ተማምኖ ለአዲስ ዘመን የሚመጥን አዲስ አመራር፣ ለቆዩና ለአዳዲስ ተግዳሮቶች ዘላቂና አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚያፈልቅ ድርጅታዊ አቅም መፍጠር ይጠበቅበታል። ይኼን ለማድረግ ትልቁ ሃብቱ አንድነቱ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ መሆን ባልቻሉበት ወቅት በአንድነት በመቆምና (በአንድነት በመሰዋት) የሕዝቡ የአንድነት ምልክትና ተምሳሌት ሆኖ እንደቆየው ሁሉ፣ አሁንም የሕዝብን አንድነት የጠበቀ ሕዝባዊ ድርጅት መስርቶ ሕዝቡን ለድል ማብቃት ይችላል። ተደራጅ። በራስህ ተማመን። ለሕዝብህ ድምፅ፣ ወኪልና ተሟጋች ሁን። ሕዝቡን ለመብቱና ለፍላጎቱ ተገዢ ሆነህ ታግለህ አታግለው። ምራው። ለሥልጣን ተወዳደር። ሥልጣን ተናጥቀህ ለሥልጣን አብቃው። ዓላማህንና ዓላማውን ለመተግበር ተንቀሳቀስ። ይሄን ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው። ታሪካዊው ወቅት አሁን ነው። ታሪካዊ ግዴታን የመሸከም ጊዜው አሁን ነው። ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር የማበርከት ጊዜው አሁን ነው።