});

መንግስት ሕዝባችንን ከጥቃት፣ ክልላችንን ከመደፈር እንድታደግ እንጠይቃለን፡፡ከኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግልጫ

ከኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግልጫ

በኦሮሚያ ምስራቅ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምዕራብ አቅጣጫዎች በሕዝቦች መሃከል የተፈጠሩት ግጭቶች መፍትሔ ሳይበጅለት የቆየ ሲሆን፤ ሰሞኑን ደግሞ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ስሙ አርቁምቤ በሚባል ቦታ በኔሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ወረዳዎች ከሚነሱ ኃይሎች በኦሮሚያ ፀጥታ አስከባሪዎች ላይ የደረሰዉን አሰቃቂ ጭፍጨፋ መድረሱን የሰማነው በታላቅ ሀዘን ነው፡፡ ፀረ አምባገነናዊ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ትግሉም በኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ማግኘት ብቻ የሚወሰን ሣይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ግፍና ጭቆና ስር የነበሩ ሕዝቦችን ያስተባበረ መሆኑን የተገነዘበዉ የገዥው ቡድን/ፓርቲ አባላት በክፉ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ ትግሉ እየተፋፋመ ባለበት ወቅት እና አብዛኛው ሕዝባችን የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን አጥቶ ልጆቹን ለማብላትም ሆነ ለማስተማር ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት ላይ ሥልጣን ከእጃቸዉ ያመለጠዉ ኃይል ወንድም ወንድሙን እንዲገድል በገንዘብ በመግዛት ሕዝብ በማጋጨት ሀገር እስከ ማፍረስ ልሄዱ እንደሚችሉ ፓርቲያችን የኦሮሞ ፈደራላዊ ኮንግረስ በየጊዜው በሚያወጣ መግለጫዎችም ሆነ ማሳሰቢያ ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ብቻ ሳንወሰን በየጊዜው እና በየቦታው የሚለኮሱ ግጭቶች በሠላማዊ እና ሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ካለን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከቆምንለት ዓላማ አንፃር ጭምር፣ በዜጎች ሁሉ ተሳትፎ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትገነባ ድርጅታችን ሲያሳስብ መቆየቱ እንደማይረሳ እምነታችን የጸና ነው፡፡ ውድ ዋጋ ስንከፍል የቆየነውም የሠላማዊ ትግል መስመር መምረጣችንም ለሠላም ያለንን እምነት ገላጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ለቆዳቸው ሲባል እንደሚገደሉ እንስሳት ሁሉ የኦሮሞ ወጣት፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ፣ እርጉዝ፣ ሕፃናት ወዘተ በየቦታው ርህራሄ በሌላቸው የመንግስት እና የየክልሎች ታጣቂዎች የሚገደሉት የኦሮሚያ ክልል ከሚገኝበት የጅኦግራፊ እና አስተዳደር አቀማመጥ አንፃር መሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ በአለፉት የኢህአደግ የአገዛዝ ዓመታት የሞቱት፣ የተሰወሩት፣ ከሀገር ሲኮበልሉ በየቦታው የአውሬ ሲሳይ ሆነው የቀሩት የዜጎች ቁጥር ለታሪክ ትተን በአለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ብቻ ከአምስት ሺ በላይ የኦሮሞ ወጣቶች በግፈኞች ተገድለዋል፡፡ በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ልጅ ተገድሎ እናት በልጇ ሬሳ ላይ እንዲትቀመጥ ተገዳለች፡፡ ከምጥ ለመገላገል ወደ ሆስፒታል እየተወሰደች ሳለች እናት በመንገድ ላይ የተገደለችዉ በዚህ በኦሮሚያ ክልል ነዉ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በጋምቤላ፣ በሼኮ መዠንገር፣ በጉራ ፈርዳ፣ በጌዲኦና በጉጂ፣ በአርባጉጉ፣ በበደኖ፣ወዘተ በሕዝቦች ላይ በግፍ እልቂት ተፈጽሟል፡፡ እንዲሁም በምስራቁ የኦሮሚያ ክፍል በኦሮሞና በሱማሌ ብሔሮች መካከል በጫሩት ግጭት የሟቾች ቁጥር ገና በውል ባይታወቅም፤ ወደ አንድ ሚሊዩን የሚጠጋ የኦሮሞ ተወላጆች የተፈናቀሉ ሲሆን በሱማሌ በኩልም የተገደለውና የተፈናቀለው ዜጋ ቁጥርም በርካታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በጂግጅጋ ከተማም ግጭቱን የሃይማኖት ለማስመሰል ቤተእምነቶች ጋይተዋል፡፡ በጌዲኦና በጉጂ ኦሮሞ መካከልም በተጫረ ግጭት በግፍ ሕይወታቸውን ከአጡት ወገኖች በተጨማሪ ከሁለት መቶ ሺ ዜጎች በላይ ተፈናቅለዋል፡፡ በቦረና ሞያሌ፣ በሐዋሳ፣ በወልቂጤ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በወልዲያ፣ በቤነሻነጉል ጉሙዝ፣ በከፈቾ፣ በራያ፣ ወዘተ ግጭቶች ተከስተዉ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰቆቃ የተጋለጡት ዜጎች አብዛኛው ያለመጠለያ በሜዳ ላይ ወድቀዉ የይድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ባሉበት ወቅት ላይ በምዕራብ ኦሮሚያ ደግሞ በኦሮሞና በቤነሻንጉል ጉሙዝ ድንበሮች አከባቢ በተጫረው ግጭት ሰበብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፤ ከሞት የተረፉት በርካታ የኦሮሞ እናቶች፣ አረጋዊያን፣ ህጻናት፣ ተፈናቅለው በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ያለመጠለያ በከፍተኛ እንግልት ላይ ይገኛሉ፡፡

ውድ ወገኖቻችን፤

በምስራቁ የሀገራችን ክፍል በሕዝቦች ላይ የተከፈተው ሽብር ካደረሰው ችግር ሳናገግም፤ በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል የተከፈተው ግዲያና ማፈናቀል አገርሽቶ፤ ሠላም ለማስከበር በተሰማራዉ የኦሮሚያ ታጣቂ ኃይሎች ላይ ሕዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ስሙ አርቁምቤ በሚባል አከባቢ በተፈጸመው ከበኔሻንጉል ጉሙዝ አከባቢ ታጣቀዉ በመጣ ወረራ ኃይል በተሰውት የኦሮሞ ዜጎች ሬሳ ላይ የተፈጸመው ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት እንኳንስ በሰለጠነዉ ዓለም ቀርቶ በጥንታዊ ገዳይ ተገዳይ መካከል ተደርጎም የማይታወቅ ድርጊት ስለሆነ ፓርቲያችን አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ኦፌኮ በቀላል ግጭቶች የሚፈጠሩ ግድያዎችን እየኮነነ፤ ግፉን የፈጸሙ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ መንግስት የሚከተሉትን እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወስድ ያሳስባል፡፡

1ኛ. የመንግስት ቀዳሚ ኃላፊነት የዜጎችን ሠላምና ፀጥታ ማስከበር ስለሆነ በየቦታው በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግደያና ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ 2ኛ. ከተጎጂ ዜጎች ለማረጋገጥ እንደተቻለዉ በኦሮሚያ እና በበኒሻንጉል አዋሳኝ አከባቢዎች ዘግናኝ ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅት በቦታው የነበሩት የመከላከያ ኃይል አባላት ጥቃቱን ማስቆም እየቻሉ ይህንን አለማድረጋቸዉ ይሰማል፡፡ ስለሆነም መንግስት የበግ ለምድ ለብሰው በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የተሰገሰጉትን ተኩላዎች በአስቸኳይ እንዲመነጥር አበክረን እንጠይቃለን፡፡ 3ኛ. በአሁን ጊዜ በሀገራች ውስጥ እየተከሰተ ያለው ችግር እጅግ ሰፊ እና ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ መንግስት እና ገዥው ፓርቲ ብቻቸውን መፍታት ስለማይችሉ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ እየታገሉ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን የሚያሳትፉበትን መንገድ በአስቸኳይ እንዲያመቻቹ እናሳስባለን፡፡ 4ኛ. በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ላይ የተጀመረው ወደ ሕግ የማቅረብ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን ለማድረግ ቃላችንን እናድሳለን፡፡ 5ኛ. በግፍ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሕይወት የማዳን ስራ እየተሰራ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት መንገድ እንዲመቻች እናሳስባለን፡፡ 6ኛ. ለሕዝባቸው ነጻነት ሲሉ ሲታገሉ ለተሰዉ፣ አካላቸው ለጎደለ፣ ቤተሰባቸው ለተበተነ፣ ንብረታቸው ለወደመ ሁሉ በቂ መካካሻ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች በተሰዉ ወገኖቻችን ስም እንጠይቃለን፡፡ 7ኛ. ግርግር በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ኃይሎችም በሀገሪቱ የተጀመረውን የነጻነት ትግል ለማኮላሸት እንደማይችሉ ተገንዝበዉ ለለውጡ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽዎ ማድረግ ተመራጭ መሆኑን የኦሮሞ ፈደራላዊ ኮንግረስ/ኦፌኮ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ የተሰዉ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፣ ቤተሰቦቻቸውንም ፈጣሪ ያጥናልን እንላለን! የኦሮሞ ፈደራላዊ ኮንገሬስ ፊንፊኔ፤ ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም.