});

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውስጥ የተፈፀመው ምዝበራና አዲሱ አወቃቀር


የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በአዲስ መልክ እንዲዋቀርና በድርጅቱ ውስጥ የተፈፀመው ምዝበራ ተጣርቶ ተጠያቂ ግለሰቦች ህግ ፊት እንዲቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ምርመራ ከተጀመረ ስንብቷል። በከፍተኛ ምስጢር ተይዞ እየተካሄደ ያለው ምርመራ እጅግ ግር የሚያሰኙና አዳዲስ መረጃዎችን አግኝቷል። ምርመራው እንደቀጠለ ሲሆን በእስካሁኑ ምርመራ ሜቴክ የንግድ አውሮፕላን ይፋዊ ባልሆነ መንገድ መግዛቱን የሚያሳይ መረጃ ተገኝቷል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ ከሀላፊነት ለቀው መቀሌ ከሰፈሩ የህወሀት ሰዎች ጋር ተቀላቅለዋል።በአዲሱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በቀለ ቡላዶ የሚመራው ሜቴክ ደግሞ የኮርፖሬሽኑን ስም ወደ ብሔራዊ የኢንዱስትሪያል ምህንድስና ኮርፖሬሽን በመቀየር ወታደራዊ ምርት የሚያመርቱ የኮርፖሬሽኑን ኢንዱስትሪዎች ለመከላከያ ሚኒስቴር በማስረከብ በአዲስ መልክ ለመደራጀት እየተንቀሳቀሰ ነው። በሜቴክ ስር ከነበሩ 14 ኢንዱስትሪዎች አራቱ ሙሉ ለሙሉ ወታደራዊ ምርትን የሚያመርቱ ሲሆን እነዚህን የማስረከቡ ስራ ተሰርቷል። አዲሱን አመራር በአግባቡ ወደ ስራ ለማስገባት ከዚህ ቀደም የተፈፀመው ምዝበራና ህገ ወጥ አሰራርን መርምሮ ሳይጨርሱና የድርጅቱን ሀብትና ኪሳራ ሳይለዩ ርክክብ መፈፀም አስቸጋሪ ሆኗል። በህወሀት ይመራ የነበረው የቀድሞው ሜቴክ የንግድ አውሮፕላን ገዝቶ እንደነበር ሆኖም የአመራር ለውጥ ሲካሄድ ግን አዲሱ የሜቴክ አመራር አውሮፕላኑን እንዳልተረከበ ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ምንጮች ሰምታለች። ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ አውሮፕላኑን በተመለከተ የተገኙ ፍንጮችን የሸሸጉትና ከምርመራው ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጫችን አውሮፕላኑ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ ለማወቅ እንደተቸገሩ ተናግረዋል። አውሮፕላኑ ያገለገለና በግዥው ወቅት እድሳት ተደርጎለት ለገበያ የቀረበ መሆኑንም መረጃዎቹ ያሳያሉ። ምርመራው ከሀገር ውጪም የሚዘልቅ መሆኑን ምንጫችን አልሸሸጉም። የቀድሞ የሜቴክ አመራሮች የአውሮፕላኑን ግዥ የፈፀሙበት ሰነድና ተያያዥ የመልዕክት ልውውጥ ሰነዶች ከአምስት ዶሴ በላይ ሆነው መርማሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እጅ ገብቷል።

ከሜቴክ ላይ የደን ምንጣሮ ውል ተቀብሎ ክፍያ ያልተከፈለው ግለሰብ ናሁ ቲቪ ላይ እንደተናገረው ሜቴክ ከመብራት ሃይል ጋር ያለምንም ጨረታ የደን ምንጣሮ ኮንትራት የተስማማው በሄክታር 48,000 ብር ነበር።

ሜቴክ ኮንትራቱን ወስዶ ጉዑሽ ካሳ ለተባለ ሶስተኛ ግለሰብ በሄክታር 13,000 ብር ስራውን ሰጠው። ጉዑሽ መልሶ ለአራተኛ ወገን ስራውን በሄክታር 6,000 ብር ሰጠው። ስራው ከስምንት እጥፍ ባነሰ ገንዘብ መሰራት ይችል ነበር ማለት ነው። ሜቴክና ሌላ በመሃል ያለ አካል በሄክታር 42,000 ብር ትርፍ ሲያገኙ ነበር። ምንም ሳይሰሩ። ከጅምሩም ስራው በጨረታ ላሸነፈ ድርጅት ቢሰጥ ምናልባትም በሄክታር ከ6,000 ብር በጣም ባነሰ ወጪም ሊሰራ ይችል ነበር። ባጠቃላይ የሚመነጠረው ደን ከታች ኮንትራቱ ላይ እንደሚታየው 123,189 ሄክታር ነው። በሄክታር 42,000 ብር በመሃል በቅብብሎሽ እንዲበላ ከተደረገ ባጠቃላይ ለመዝረፍ ታቅዶ የነበረው 123,189 x 42,000 ብር = 5.2 ቢሊዮን ብር ነበር ማለት ነው። ምንም ሳይሰሩ 5.2 ቢሊዮን ብር።

ዋልታ የሰራው ዶኩመንታሪ ላይ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ ሜቴክ "እየሰራን እንማራለን እየተማርን እንሰራለን" በሚል የህዳሴው ግድብ ስራዎችን መውሰዱ አግባብ አይደለም ብሎ ነበር። ናሁ ቲቪ ባለፈው ሳምንት ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውን ስለዚህ አስተያየት ምን ትላለህ ሲለው "የትም ሀገር ሰው እየተለማመደ ነው የሚሰራው አለ"። ሜ/ጀ ክንፈ ይሄን ሁሉ ገንዘብ ካላግባብ መዝረፉና ማዘረፉ ሳያንሰው.....። ዚህ በተጨማሪ በሜቴክ ወጪ የተገዙ ሁለት መቶ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውንና በቤቶቹ ውስጥም የተለያዩ ግለሰቦች እየኖሩበት መሆኑን መርማሪዎች በማስረጃ ደርሰውበታል። በሜቴክ ስም ያሉትን የቤቶቹን ካርታዎች ድርጅቱ ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ስምተናል። በምርመራው ወቅት ከተሰባሰቡት መረጃዎች ዋና ዋናዎቹን ዘጋቢያችን ተመልክቷል። ኢትዮ ፕላስቲክ የተባለውን ኩባንያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲረከብ ኩባንያ ወደ ኮርፖሬሽኑ የገባበት መንገድ ብዙ የገንዘብ ዝርፊያ የተፈጸመበት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ሆኖ ተገኝቷል። ሜቴክ ኢትዮ ፕላስቲክን በወቅቱ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የገዛበት ትክክለኛ ዋጋ 128 ሚሊየን ብር ነው።ሆኖም ኢትዮ ፕላስቲክ ወደ ሜቴክ በተጠቃለለበት ሂደት ወስጥ ከሚያወጣው ዋጋ በላይ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ እላፊ ገንዘብ 188 ሚሊየን ብር ወጭ ተደርጓል።የዚህ ገንዘብ መዳረሻም አልታወቀም። የሜቴክ ዕዳን ማን ይረከበው? ሜቴክ ውስጥ የነበረው መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ብክነት የኮርፖሬሽኑ ርክክብ ላይ እጅግ ከፍተኛ ችግር መደቀኑ ተነግሯል።በሌላ በኩል የቀድሞ ሜቴክ ላይ የነበሩ አመራሮች ለቀቁ እንጂ ኮርፖሬሽኑ ውስጥ እስከታችኛው ተዋረድ የነበሩ ሰዎች አሁንም አሉ። በዚህም ምክንያት አዲሶቹ የኮርፖሬሽኖቹ አመራሮች የሚቀርቡላቸው ገንዘብ ነክ ሰነዶች ላይ ከመፈረም በእጅጉ እየተቆጠቡ ነው። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን የመፍታቱ ሂደትም አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል። እርግጥ ሜቴክ ግድቡ ላይ ለመስራት ውል ወስዶ ከነበራቸው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ከብዙው መውጣቱ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን መዘገቡ ይታወሳል። ሜቴክ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የሚሰራው ስራ በተወሰኑ የስቲል ስትራክቸር ስራዎች ላይ የተገደቡ ስራዎችን ብቻ እንዲሆንም በመንግስት ተወስኗል። ሜቴክ ከህዳሴው ግድብ ኮንትራት ሲወስድ ጥቅል ዋጋው የ25 ቢሊየን ብር ነው።ከዚህ ውስጥ 16 ቢሊየን ብሩ ተከፍሎታል።ይህም የክፍያው ከ65 በመቶ በላይ መሆኑ ነው።ሜቴክ ግን የፕሮጀክቱን 30 በመቶ ያላለፈ ስራ ነው ያከናወነው ተብሏል። ታዲያ ሜቴክ ለኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው የተከፈለውን ገንዘብ ልዩነት እንዴት መልሶ ርክክብ እንደሚፈጽም አልታወቀም። አሁን ያለው የሜቴክ አመራር እየተረከበ ያለው ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም ከነበረው ያነሰና ዕዳ የተሸከመ ተቋም ነው። ሜቴክየተቋቋመው በ10 ቢሊየን ብር የተፈቀደና በአራት ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል ነው ። እንደ ደጀን አቪዬሽን አይነት ወታደራዊ ምርት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ከመዞራቸው ጋር በተያያዘና በብዙ ፋብሪካዎች የንብረት ጉድለት በመታየቱ ርክክቡን አስቸጋሪ አድርጎታል። ርክክቡ ሙሉ ለሙሉ ሊፈጸም የሚችለውም መንግስት ኪሳራውን ተቀብያለሁ ብሎ እስከፈቀደ ድረስ ይሆናል።