});

ፓርቲዎቹ በድርድሩ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በምልተ ጉባኤው ነጥቦች ላይ ተስማሙበአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ስብሰባ የትኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድሩ ላይ ይሳተፉ በሚለውና በድርድሩ ምላተ ጉባኤን በሚመለከቱ ሁለት ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል ።

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባለፈው ሳምንት ከቀረቡት 12 የረቂቅ ነጥቦች ውስጥ በፓርቲዎቹ የድርድር ዓለማ ላይ መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት በሁለት ነጥቦች ላይ በመስማማት የዛሬውን ስብሰባቸውን አጠናቀዋል ።

በዛሬው ውይይት በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር የትኞቹ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ በሚለው ነጥብ በአገሪቱ ፍቃድ ያለውና ከኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ሰርትፍኬት ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድርድሩ መሳተፍ እንደሚችል ሁሉም ፓርቲዎች ተስማምተዋል ።

ድርድሩን በሦስት መልኩ ለማድረግ ስምምነት የተደረሰበት ሲሆን አንደኛው ገዥው ፓርቲ የጋራ አጀንዳ ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቡድን ጋር ፣ ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ የተለየ አጀንዳ ካለው ፓርቲ ጋር እና ገዥው ፓርቲ ከ21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የሚያካሂደው ድርድር ይሆናል ።

ገዥው ፓርቲ ከ21 የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በሚደራደርበት ወቅት የተሳታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ሁለት ሦስተኛ ቁጥር መገኘው እንደሚኖርበነት በውይይቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል

በመጨረሻም በውይይቱ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ወቅት ማን አደራዳሪ እንደሚሆን አከራካሪ ሆኖ የተገኘ ሲሆን ይህ ነጥብ በሚቀጥለው ስብሰባ ወቅት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ቀጥሮ ተይዟል ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች አደራዳሪን በተመለከተ የሴማያዊና መድረክ ፓርቲዎች ገለልተኛና ሦስተኛ የሆነ አደራዳሪ ድርድሩን እንዲመራ መደረግ እንዳለበት ሓሳብ የሠጡ ሲሆን ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ፓርቲዎች በራሳቸው በዙር የማደራደር ሚና መጫወት ይችላሉ ብለዋል ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቀጣይ ውይይታቸውን በቀጣይ ሳምንት ለማድረግ ተስማምተዋል ።