});

ጠ/ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ጋር ተወያዩጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል ተብሏል።

በተለይም ኢትዮጵያና አሜሪካ በንግድና ኢንቨስትመንት የበለጠ ተቀራርበው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሜሪካ ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ተግባር የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ያላት ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ የቀጠናው ሠላም እንዲረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በዚህ ወቅት ገልጸዋል።

ረዳት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍም ነው የተናገሩት።

ሃገራቸው ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው መደሰቷንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

በቀጣይም አሜሪካ ከኢፌዴሪ መንግስት ጋር ተባብራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

ረዳት ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

አምባሳደር ያማማቶ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በቀጣይ ጊዜያት ለመወያየት እቅድ መያዛቸውን መግለጻቸውም ይታወሳል።

መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነው፤