});

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከሐምሌ 4 እስከ ሐምሌ 7 2008 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል


የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከግንቦት 22 ጀምሮ ለአራት ቀናት ሊሰጥ የነበረው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በፈተና ወረቀቶች መውጣትና ቀድሞ በማህበራዊ ድህረ ገፅ መሰራጨቱን ተከቶሎ ፈተናው መቋረጡንና የድጋሚ ፈተና ቀን ከሰኔ 27-30/2008 ዓ.ም እንደሚሰጥ ለህዝብና ለተፈታኝ ተማሪዎች ማሳወቁ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁንና ይህ ጊዜ ከረመዳን ፆም ወር ጋር የተገናኘ መሆኑን በመግለፅ የኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለተማሪዎች ከፆም በኋላ እንዲሆን ያቀረበውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ከክልሎች ጋር በተደረገው ምክክር ጥያቄው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃሳብ መሆኑን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለመገንዘብ መቻሉን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ሌሎች ተማሪዎችና ወላጆቻቸውም የጓደኞቻቸውንና የወላጆቻቸውን ጥያቄ ይጋሩታል የሚል እምነት በመያዝ ፈተናው ከሐምሌ 4 ሰኞ እስከ ሐምሌ 7 ሐሙስ 2008 ዓ.ም ድረስ እንዲሰጥ መወሰኑን ትምህርት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሁሉም ዝግጅቶች በተሟላና በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተፈፀሙ መሆኑንና በእለቱ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ሁሉም ተማሪዎች የመለያ ካርዳቸውን /ID - Card/ በመያዝ በተመደቡበት ትምህርት ቤታቸው እንዲገኙ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አስተላልፋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውንና መምህራንን በማስተባበር ተማሪዎች በተረጋጋ መንገድ የትምህርት ክለሳ እንዲያደርጉ፣ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙና እንዲያደርጉ እንዲሁም ወላጆችም ቀጣዩን አንድ ወር ልጆቻቸውን እንዲደግፉ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪውን አስተላልፏል፡፡