});

ከስራ በሁዋላ አየሁዋት ሄድኩና

ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ እንዲከበር ያደረገ ደርግ ነው፤ ከዛ በፊት ስራ የተናቀ ተግባር ነበር፤

“ዋይ ዋይ ባላባት እንግዲህ ቀረ ሳይሰሩ መብላት “ ይሉ ነበር የዩኒቨርስቲ ፋኖዎች!

ደርግ ስራን አስከበረ፤ አንዳንዶች እንደውም ባንድ ጊዜ ሁለት ስራ ደርበው እሚሰሩ ነበሩ ! ለምሳሌ አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ሩጫ ልምምድ ሲያደርግ እግረመንገዱን በየቤቱ ፖስታ ያድል ነበር! በደርግ ብር ኖቶች ላይ ያሉትን ምስሎች ተመልከቷቸው ! ሰፌድ የምትሰፋ ሴት፤ የሚመራመር ሳይንቲስት ! ቡና የሚለቅም ገበሬ! የቦዘነ የለም!

መንግስቱ ሃይለማርያም እልል ያለ አምባገነን ነበር ፤ በስራ ግን ቀልድ አያውቅም! የሆነ ጊዜ ላይ መንጌ፤ አለማየሁ እሸቴንና ጥላሁን ገሰሰን ወደ ቢሮው አስጠራቸው !

“ ወጣት አለማየሁ! “ “አቤት ጏድ ሊቀመንበር “

“እጅ እግሩ ተቆርጦ አከላቱ ጎሎ ይኑር አባብየ እየበላን ቆሎ አርባራቱን ታቦት ጠርቶና ለምኖ ብለው የዘፈንከው ምን አስበህ ነው? አባትህ ካልሰራ ማን የቆላውን ቆሎ ነው የሚበላው?"

“ ጏድ ሊቀመንበር ይሄን ዘፈን የዘፈንኩት ካብዮቱ በፊት ባድሃሪው ስርአት ውስጥ ነው! አሁን ንቃቴ ከጨመረ በሁዋላ የገዛ ዘፈኔን ሳደምጠው ሼም ይጨመድደኛል” አለ አሌክስ ዞማ ፀጉሩን በጣቶቹ እየቆፈረ !

“ ሂስህን ከዋጥህ ላይቀር፤ ጥቂት ስንኞችን አስተካክለህ በድጋሚ ብትዘፍነው ምን ይመስልሃል?”

“ ጥሩ አሳብ ነው ጏድ ሊቀመንበር ! ምኑጋ ላስተካክለው? ”

መንጌ በመስኮቱ አሻግሮ ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ ፤” እጅ እግሩ ተቆርጦ የሚለው ስንኝ በጣም ዘግናኝ ነው ! የምር አባትህ ከሆነ ትንሽ አስተያየት አድርግለት ! ወይ እጁን ወይ እግሩን አስቀርለት ! "

“ የትኛውን ላስቀርለት?” አለ አሌክስ !

“ እንደኔ እንደኔ እጁን ብታስቀርለት ጥሩ ነው፤” ቀጠለ መንጌ” የለመነውን ቆሎ ለመያዝ ራሱኮ እጅ ያስፈልገዋል፤ እንደ ሁኔታው አይተን፤ ብሄራዊ ውትድርና ላይም ልናሳትፈው እንችላለን ፤ ሻእቢያ ናቅፋ ላይ የረፈረፈችን እግር የሌላቸው ሸሽተው እማያመልጡ ወንበዴዎችን የቀበሮ ጉድጏድ ውስጥ ወትፋ ነው፤ ‘ ይገርምሃል መጀመርያ ፈንጅ በእግራቸው ያስጠርጏቸዋል! ከዛ ደግሞ በባሊ ተሸክመው ወስደው ሽምቅ ውጊያ ላይ ያሰማሯቸዋል! አገር መገንጠል የተለማመዱት የገዛ ወንድሞቻቸውን እግር በመገንጠል ነው! ርጎሞች!"

ቀጥሎ መንጌ ወደ ጥላሁን ገሰሰ ዞር ብሎ " እሺ ጃል ጥላሁን! ወዳንተ ስመለስ፤

-ያላየሁሽለታ በማዘን፤ በጭንቀት በድቀት ተክዤ ሌሊቱን ሳልተኛ እያደርኩኝ፤ ቀኑን እውላለሁ ፈዝዤ-

ብለህ የዘፈንከውን አዳምጫለሁ! አሁን ያለንበት ሁኔታ የሙሉ ጊዜ አፍቃሪነትን የምናበረታታበት አይደለም!! ወጣቱ ቀን በስራ ተስማርቶ ማታ ላይ በሃሳብ መፍዘዝ መብቱ ነው! በተረፈ ኢትዮጵያ ሌትም ቀንም በፍቅር የሚጃጃል ወጣት የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም! የወዝ አደር እንጂ የውዝዋዜ አደር ፓርቲ ለመገንባት አልተነሳንም! ተግባባን?”

ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ ጥላሁን ገሰሰ “ ፈልጌ አስፈልጌ “ የሚለውን ዘፈን ሰራ! ዘፈኑ የመንጌ ተፅእኖ እንዳለበት ለማወቅ እኒህን ስንኞች ብቻ ማየት ይበቃል!

“ አየሁዋት መርካቶ ሲሉኝ ትናንትና ከስራ በሁዋላ አየሁዋት ሄድኩና ከስራ በሁዋላ ብቅ ብል በማታ የለችም ካዛንችስ እሱዋ የት ተገኝታ እሷ የት ተገኝታ ! “