});

በከባድ መስዋዕትነት የተገኘ ለውጥ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ኣይደናቀፍም (የኦነግ መግለጫ – መስከረም 20, 2018ዓምበኣሁኑ ወቅት በኦሮሞ ነጻነት ግንባርና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ከኣንድ ወር በፊት በተደረሰው ስምምነት መሰረት በመካከላቸው የነበረው ጦርነት ቆሞ፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሰላማዊ መንገድ በመታገል የፖለቲካ ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ወደ ስራ ገብቷል። በዚህም የድርጅቱ ከፍተኛ ኣመራር በሊቀ-መንበሩ ኣቶ ዳውድ ኢብሳ በመመራት መስከረም 15 ቀን 2018ዓም የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፡ ፊንፊኔ መግባቱ ይታወሳል። በዚህ የኦነግ ከፍተኛ ኣመራር የኣቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በመውጣት ደስታውን መግለጹንም በኣያሌ የሃገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች ሲዘገብ ነበር፥ በመዘገብ ላይም ይገኛል። ይህ ታላቅና ታሪካዊ የኣቀባበል ስነ-ስርዓትም ህዝባችን ለኦነግና ለዓላማው ያለውን ፍቅርና ድጋፍ እንዲሁም ተስፋ ቁልጭ ኣድርጎ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም በበኩሉ ከኦነግ ጋር የእርቅ ስምምነት ከማድረግ ኣንስቶ ለዚህ ታላቅና ታሪካዊ የኣቀባበል ስነ-ስርዓት ሁኔታዎችን እስከማመቻቸትም ይሁን ከዚያ ወዲህ እያሳየ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን የሰላምና የእርቅ ሂደት ለማሳካት ትልቅ ፍላጎት እንዳለውና ዝግጁ መሆኑን የምያረጋግጥ ነው ብለን እናምናለን። ባጠቃላይ በኣሁኑ ወቅት በሁለቱም ወገን (የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኢትዮጵያ መንግስት) እየታየ ያለው ሁኔታ ለረዥም ዓመታት ኢትዮጵያን የብጥብጥ፣ የረሃብና የድህነት ምንጭ ሲያደርጋት የነበረዉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ታላቅ ተስፋ ያስሰነቀ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ተስፋ ሰጪ ለውጥ ደግሞ በነጻ ወይም በስጦታ ሳይሆን በከባድ መስዋዕትነት የተገኘ ስለመሆኑ ማንም ሊክደው የማይችል ሃቅ ነው። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መንግስትና በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተጀመረው ይህ የሰላምና የእርቅ እንቅስቃሴ እንዲደናቀፍ የሚጥሩ ኣንዳንድ ግለሰቦች፣ ኣካላትና የፖለቲካ ሃይሎች ዛሬም ኣልታጡም። በዚህም ባለፉት ጥቂት ቀናት በፊንፊኔ ከተማና በሌሎችም ኣንዳንድ ቦታዎች ኣላስፈላጊ ረብሻ በመቀስቀስ ህዝቦችን ለማጋጨት ጥረት ስደረግ ተስተውሏል። ይህን መሰሉ ድርጊት ከኦነግ የኣመራር ኣካል የኣቀባበል ስነ-ስርዓት ጋር ተያይዞ መፈጸሙ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ነጻነቱንና የሃገር ባለቤትነት መብቱን ለመጎናጸፍ እያካሄደ ያለውን ፍትሃዊ ትግል ስም ለማጉደፍና በሌሎች ዘንድ በጥርጣሬና በፍርሃት እንድታይ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ የምያመላክቱ በርካታ ማሳያዎች ኣሉ። “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል!” እንደሚባለው ይህንን ሴራ የፈጸሙት ኣካላት ለዚህ ኣስነዋሪ ድርጊታቸው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጣታቸውን በመቀሰር በሚድያዎችና በተለያየ መንገድ ኣፍራሽ ፕሮፓጋንዳን በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ እያየንና እየሰማንም ነው። ይህን በመሰለው ኣፍራሽና እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩት ኣካላትና ሚዲያዎች ከዚህ ድርጊታቸው በኣስቸኳይ እንዲታቀቡ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኣካላት ሁሉ ሃላፊነታቸውን መወጣት ያስፈልጋል። ህዝባችንም በመሬት ላይ ያለውን እውነታ (የለውጥ ተስፋውንና ይህንን ተስፋ ለማጨለም እየተሸረበ ያለውን ሴራ ሁሉ) በሚገባ ተከታትሎ መገንዘብ ኣስፈላጊ ነው። እውነተኛ እርቅና ዘላቂ ሰላምን ለማስገኘት ከሚሰሩ ሃይሎችና ኣካላት ጋር ኣብረን ቆመን ከዚህ በተቃራኒዉ በመሆን በለዉጡ ሂደት ላይ ተንኮል የሚሸርቡትን ሃይሎችና ኣካላት ሴራ ማጋለጥና ማምከን የሁላችንም ግዴታና ሃላፊነት መሆን ይገባዋል። ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲና ዘላቂ ሰላም የሚያሸጋግር የለውጥ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሊሳካ የሚችለው ሁላችንም ሃላፊነታችንን ከተወጣን ነው ብለን እናምናለን። በዚህ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያን መንግስት ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሃይሎችና ኣካላት ሁሉ ጋር በውይይትና በመግባባት መስራቱን ኣጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለሁሉም ያረጋግጣል። በመጨረሻም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላትና ደጋፊዎች፣ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞና ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ባጠቃላይ በማናቸውም ሃይሎችና ኣካላት ትንኮሳ ኣላስፋላጊ ንዴትና ስሜት ውስጥ ከመግባት እየተቆጠቡ በሚያጋጥሙ ሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ድርጅቱ የሚያስተላልፈውን መመሪያና ውሳኔ በስራ ለመተርጎም እንዲጥሩ ኦነግ መልዕክቱን ያስተላልፋል። በከባድ መስዋዕትነት የተገኘ ለውጥ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ኣይደናቀፍም ድል ለኦሮሞ ህዝብ ! የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መስከረም 20, 2018ዓም