});

በኦሮሚያ የስራ ማቆም አድማ ተጀመረከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ማክሰኞ የስራ ማቆም አድማ መጀመሩን ነዋሪዎች አስታወቁ።

በአምቦና ጉደር አካባቢ የንግድ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች መስጫ ተቋማት የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ መሆናቸውን በጉዳዩ ዙሪያ ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

መንግስት በክልሉ እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየወሰደ ያለውን ግድያና አፈና በመቃወም የስራ ማቆም አድማው መጀመሩን እማኞች የገለጹ ሲሆን፣ የመንግስት አካላት አድማው እንዳይካሄድ ያደረጉት ዘመቻ አለመሳካቱን ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ማክሰኞ የስራ ማቆም አድማው ላይ በሚሳተፍ የንግድ ተቋማት ላይ እስከ አምስት ሺ ብር የሚደርስ ቅጣትን ለመጣል ማሳሰቢያን ቢሰጥም፣ ሁሉም ድርጅቶች ማክሰኞ በአድማው ተሳታፊ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ነዋሪዎች የወሰዱትን ዕርምጃ ተከትሎ የየከተሞቹ የንግድ ቢሮዎች የንግድ ተቋማት ላይ “ታሽጓል” የሚል ወረቀት እየለጠፉ ሲሆን፣ ከአምቦ ወደ ጉደር ከተማ ለመንግስት ስራ በየዕለቱ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ማክሰኞ የስራ እንቅስቃሴያቸው መስተጓጎሉን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ እማኞች አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በነቀምቴ ከተማና አካባቢው ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ ማክሰኞ መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

በአምቦና ጉደር ከተሞች ያለውን የስራ ማቆም አድማ መንግስት ሊቆጣጠረው አልቻለም ሲሉ የተናገሩት ነዋሪዎች ህዝቡ ሰላማዊ ተቃውሞን አጠናክሮ ለመቀጠል እና የተለያዩ ስልቶችን ለመጠቀም እራሱን እያስተባበረ እንደሚገኝ አክለው አስታውቀዋል።

በተያያዘ ሁኔታም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የአዲስ አመት የበዓል ዝግጅት ከተለመደው ጊዜ የቀዘቀዘ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።